top of page

ታላቁ ተልዕኮ

“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥

ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ

እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28፡ 19-20)

ጌታ ከትንሳዔው በኋላ ለቤተ ክርስቲያን “ታላቁ ተልዕኮ” በመባል የሚታወቀውን ትዕዛዝ

ሰጥቷታል። ታላቁ ተልኮ ወንጌልን የመስበክና ሰዎችን የጌታ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልዕኮ

ነው። ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ይህንን ተልዕኮ በምድር የመቀመጧ ዋና ግብ አድርጋ መውሰድ

ይኖርባታል። በቤተ ክርስቲያን የምናደርጋቸው ሁሉ ለታላቁ ተልዕኮ የሚያዘጋጁን መሆን

ይገባቸዋል። ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን መስበክና የዳኑትን ደግሞ ደቀ መዛሙርት ማድረግን ቸል

ካለች ዋና ተልዕኮዋን ዘንግታለች ማለት ነው።

አንደኛ፦ ትዕዛዙ “ሂዱ” የሚል ነው። ታላቁ ትልዕኮ በቤተ ክርስቲያን አራት ግድግዳ

የሚከለል ሳይሆን የመውጣት አገልግሎት ነው። የስራው ስፍራ መስክ ነው። ተልዕኮው ሰዎች ወደ

እኛ እንዲመጡ እንድንጠብቅ ሳይሆን እኛ ወደ ሰዎች እንድንሄድ ነው። በመሆኑም ታልቁ ተልዕኮ

የሚፈጸመው ወደ አልዳኑት በመሄድ ነው። የምንሄደው ደግም “ከኢየሩሳሌም” ጀምሮ ነው። የኛ

“ኢየሩሳሌም” ያለንበት አካባቢ ነው። ለዚህ የግድ ወደ ሌላ አገር መሄድ አያስፈልገንም።

በዙሪያችን ያሉትን ለመድረስ ከተጋን ያ “መሄድ” ነው። አንዳንድ ጊዜ የምንሄደው ወደ ቤተሰብ

አባሎቻችን ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የምንሄደው ወደ ጎረቤቶቻችን ሊሆን ይችላል።

እንዳንድ ጊዜ የምንሄደው አጠገባችን ወዳለው ፓርክ ሊሆን ይችላል። ቁብ ነገሩ መሄድ ነው።

ሁለተኛ፦ ትዕዛዙ ለሌሎች ምስክር መሆን ነው። ጌታ ለሐዋሪያቱ መንፈስ ቅዱስን

ከተቀበላችሁ በኋላ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ ነው ያላቸው። (ሐዋ. 1፡8) ምስክር ያየውን፣ የሰማውን፣

የቀመሰውን የሚናገር ነው። ምስክርነት እንደዛች ሳምራዊት ሴት “ኑ ጉዴን የነገረኝን እዩ” ብሎ

መናገር ነው። የኛ ኃላፊነት የጌታን ማዳን መመስከር ነው። ሰዎችን ወቅሶ ወደ ንስሃ ማምጣት

የመንፈስ ቅዱስ ስራ ነው።

ሶስተኛ፦ የዳኑትን ደግም ደቀ መዛሙርት ማድረግ የቤተ ክርስቲያን ሃላፊት ነው። ደቀ

መዝሙር ተከታይ ነው። የዳኑት የቃሉን ወተት ጠጥተው ማደግ አለባቸው። አለበለዚያ ቤተ

ክርስቲያን የሕጻናት ክርስቲያኖች መዋያ ትሆናለች። ወንጌልን መመስከር አንድ ነገር ነው፤ የዳኑትን

ማሳደግ ደግም በጣም አስፈላጊ ሌላ ነገር ነው። ያ ሲሆን የዳኑት በቤቱ ይተከላሉ፣ ያድጋሉ፣

ሃላፊነትን ይሸከማሉ፣ ያፈራሉ።

በመጨረሻ፦ ትዕዛዙ ተስፋ ያለው ነው። ጌታ ትዕዛዝ ብቻ አይደለም የሰጠን። ነገር ግን

እስከ መጨረሻው ድረስ ከኛ ጋር እንደሚሆን በቃሉ ተስፋ ሰጥቶናል። ቃሉ የታመነ ነው።

ወንጌሉን ይዘን ስንወጣ ሁልጊዜ ጌታ ከኛ ጋር ይወጣል። ወንጌሉን ይዘን ስንሰደድ ጌታ ከእኛ ጋር

ይሰደዳል። ወንጌሉን ይዘን ብንታሰር ጌታ ከኛ ጋር በእስር ቤት ይሆናል። በሰማይና በምድር

ስልጣን የተሰጠውን የትንሳዔውን ጌታ የሚያቆም ማንም ስለሌለ ወንጌሉን ሊያቆም የሚችል

የለም። እንግዲህ ይህ ታላቅ ተስፋ ስላለን ሁላችንም ለሚሽን እንውጣ። ጌታ ይባርካችሁ።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page