ጸሎት አስተምረን -- መንግስትህ ትምጣ (ክፍል አራት)
“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥
ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ
እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... መንግስትህ ትምጣ ...” (ሉቃ. 11፡1-2)
ጌታ ባስተማረን ጸሎት አስቀድመን የእግዚአብሔርን አባትነት በመረዳት በልጅነት
መተማመን በፊቱ እንቀርባለን። በመቀጠልም የእግዚአብሔር ስም በሕወታችን እንዲቀደስ
(በእምነትና በልምምድ የእግዚአብሔር ስም በሕይወታችን ተገቢውን ስፍራ እንዲይዝ)
እንጸልያለን። ሌላው በዚህ ጸሎት ማእቀፍ ውስጥ የምናየው ሃሳብ “መንግስትህ ትምጣ” የሚለውን
ነው።
በመንፈሳዊው አለም ሁለት መንግስታት አሉ። የእግዚአብሔር መንግስት አለ፤ የሰይጣን
መንግስት አለ። ጌታችን በምድር አገልግሎቱ ስለ ሁለቱ መንግስታት አስተምሯል። በሉቃስ 12 ላይ
እንደምናነበው ፈሪሳውያን ጌታን “በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ” አጋንንትን ያወጣል በማለት
ከሰሱት። ጌታ ግን አሳባቸውን አውቆ “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች ...
ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት
ትቆማለች?... እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ
የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።” (ቁ. 25፣ 26፣ 28) በዚህ ስፍራ በግልጽ
እንደምናነበው ሰይጣን የሚሰራበት የጨለማ መንግስት አለ። ደግሞም የእግዚአብሔር ሃሳብ
የሚከናወንበት የእግዚአብሔር መንግስት አለ። የሰይጣን መንግስት ከእግዚአብሔር መንግስት
ተጻራሪ የሆነ የክፋት መንግስት ነው። የእግዚአብሔር መንግስት በምትገዛበት ስፍራ የሰይጣን
መንግስት የመስራት አቅም የለውም። ተሸናፊ ነው። ስለዚህ ነው ጌታችን “እኔ ግን በእግዚአብሔር
መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች”
በማለት ያስተማረን።
ወንጌላችን የእግዚአብሔር መንግስት ወንጌል ነው። ወንጌል ወደ እግዚአብሔር መንግስት
የምንገባበት መንገድ ነው። እኛም ወንጌሉን የተቀበልን የእግዚአብሔር መንግስት ልጆች ነን። የዚህ
መንግስት ራስ እግዚአብሔር ነው። ስርዓቱ ጽድቅ ነው። ይህ መንግስት በመጨረሻ ሁሉን አሸንፎ
የሚገዛ፣ ሌሎች መንግስታትን ሁሉ እንደ ገላባ የሚያደቅ መንግስት ነው። የእግዚአብሔር
መንግስት በሚገዛበት ስፍራ ሁሉ የእዚአብሔር ህልውና አለ። በዚያ ስፍራ የጨለማ መንግስት
ስፍራ ይለቃል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት
ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” (ማቴ. 6፡33) ይለናል። ስለዚህም ነው
በአባታችን ሆይ ጸሎት የእግዚአብሔር መንግስትን በመፈለግ የምንጸልየው። (ይቀጥላል)