top of page

ጸሎት አስተምረን -- መንግስትህ ትምጣ —ጽድቅ (ክፍል ሰባት A)

“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... መንግስትህ ትምጣ ...” (ሉቃ. 11፡1-2)

የእግዚአብሄር መንግስት አንደኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ ናት። ሁለተኛ የእግዚአብሔር ሰላም ናት። ሶስተኛ በመንፈስ ቅዱስ የሚሆን ደስታ ናት። (ሮሜ 14፡17) እንግዲህ የእግዚአብሔርን መንግስት ስንፈልግና መንግስትህ ትምጣ ስንል እየፈልግን ያለነው የግዚአብሔርን ጽድቅ፣ ሰላምና በመንፈስ ቅዱስ የሚሆንን ደስታ ነው።

የግዚአብሔር መንግስት የጽድቅ መንግስት ናት። የግዚአብሔር መንግስት ዜጎች እግዚአብሔር የሚቀበለውን ጽድቅ ያገኙ ናቸው። በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለው በራሳችን ስራ ለማግኘት የምንሞክረው “ጽድቅ” አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ፊት ማንም ጻድቅ እንደሌለ ያረጋግጥልናል። (ሮሜ 3፡11) በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለውና ሰውን ሊያጸድቀው የሚችለው ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የሚያገኘው ጽድቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጽድቅ ሲናገር “አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል” ይላል። (3፡21) ይህንን የእግዚአብሔርን ጽድቅ የምናገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ነው። (3፡22)

አሁን በእግዚአብሔር መንግስት ስንኖር በተቀበልነው ጽድቅ እንድንመላለስ የእግዚአብሔር ሃሳብ ነው። በክርስቶስ በማመን ጸድቀናል። ስለጸደቅን ደግሞ በጽድቅ ሕይወት እንመላለሳለን። ይህ ማለት እግዚአብሔር የሰጠንን ስፍራ በሚመጥን ሕይወት መኖር ማለት ነው። ጽድቅ በሕይወት የሚገለጥ ፍሬ አለው። (ፊል. 1፡9-11) ሐዋሪያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንደመከረው ጽድቅ የምንከታተለው ጉዳይ ነው። አንዱ ጽድቅን የምንከታተልበት መንገድ ደግም ለጽድቅ ምክር የሚጠቅሙትን ቅዱሳት መጽሕፍት (ማለትም ቃሉን) በመመገብ ነው። ሌላው የተቀበልነው ጽድቅ ሕይወታችንን እንዲገዛና በኛ እንዲገለጥ ጸጋ መጠየቅ ይኖርብናል። የጽድቅ ሕይወት ከእምነት ወደ እምነት እያደገና የበለጠ እየተገለጠ የሚሄድ ሕይወት ነው። (ሮሜ. 1፡17) ጽድቁን በእምነት መቀበላችን የመጀመሪያው ደረጃ ሲሆን፤ በቤቱ ስንመላለስ ደግም የጽድቅ ሕይወት እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ ኑሮ ይገለጣል። በመሆኑም የእግዚአብሔር መንግስት እንድትመጣ ስንጸልይ የጸሎቱ አንዱ ገጽታ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የተቀበልነው የጽድቅ ሕይወት እንዲገለጥና እንዲገዛ ጸጋን መጠየቃችን ነው። የእግዚአብሔር ጽድቅ ተጽኖ ያመጣል። ልክ ብርሃን በጨለማ እንዲሚያበራ የግዚአብሔር ጽድቅ በሓጢያት ጨለማ ውስጥ ላለው አለም የማብራት አቅም አለው። የግዚአብሔርን ጽድቅ ስንፈልግ በረከቱ ታገኘናለች። (ይቀጥላል)


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page