top of page

ጸሎት አስተምረን -- መንግስትህ ትምጣ —ጽድቅ (ክፍል ሰባት-B)

“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... መንግስትህ ትምጣ ...” (ሉቃ. 11፡1-2)

የእግዚአብሄር መንግስት አንደኛ የእግዚአብሔር ጽድቅ ናት። ሁለተኛ የእግዚአብሔር ሰላም ናት። ሶስተኛ በመንፈስ ቅዱስ የሚሆን ደስታ ናት። (ሮሜ 14፡17) እንግዲህ የእግዚአብሔርን መንግስት ስንፈልግና መንግስትህ ትምጣ ስንል እየፈልግን ያለነው የግዚአብሔርን ጽድቅ፣ ሰላምና በመንፈስ ቅዱስ የሚሆንን ደስታ ነው። ባለፈው ሳምንት የግዚአብሔር መንግስት የጽድቅ መንግስት ናት የሚለውን ሃሳብ አይተናል። የግዚአብሔር መንግስት ዜጎች እግዚአብሔር የሚቀበለውን ጽድቅ ያገኙ ናቸው። ዛሬ ደግሞ የእግዚአብሔር መንግስት የእግዚአብሔር ሰላም እንደሆነ እናያለን።

እግዚአብሔር ሆይ መንግስትህ ትምጣ ብለን ስንጸልይ በአንድ መልኩ በመንግስቱ ውስጥ ያለውን ሰላም መፈለጋችን ነው። የእግዚአብሔር መንግስት ወንጌል ሰላም ይሰጣል። ጌታ ኢየሱስ በቃሉ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም” ብሎናል። እዚህ ላይ እንደምናያየው ሁለት አይነት ሰላም አለ። አለም የሚሰጠው በጊዚያዊ ነገሮችን ላይ የተመሰረተ ሰላም አለ። ሁለተኛ ጌታ የሚሰጠው ሰላም አለ። አለም የሚሰጠው ሰላም ውጪያዊ ነው። ከውጭ ባሉ ነገሮች ሁኔታ የሚወሰን ነው። የጌታ ሰላም ግን ከውስጥ የሆነ ሰላም ነው። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በእርጋታ እንድንቀመጥ የሚያደርገን የእግዚአብሔር ሰላም ነው። ስለሆነም የእግዚአብሔር ሰላም በአለም እንዳለው ሰላም የነውጥ አለመኖር ብቻ ሳይሆን ዙሪአችንም ነውጥ ቢኖርም እንኳ በእርጋታ መቀመጥ ማለት ነው። የእግዚአብሔር ሰላም ሲኖረን ልባችን አይታወክም፣ አይፈራም። ስለዚህ ነው ዘማሪው “ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም” ያለው። (መዝ. 46፡2) የሰላማችን ምንጭ እግዚአብሔር እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። በማንኛውም ሁኔታ በጸሎትና በልመና ከምስጋናም ጋር ወደ እርሱ ስንቀርብ እርሱ አእሞሮን ሁሉ በሚያልፍ ሰላም ልባችንና ሃሳባችንን ይጠብቃል። በመከራ መኃል፣ በችግር መኃል አዕሞሮአችን በሰላም የተጠበቀ ነው። ጌታችን የሰላም አለቃ ነው። እውነተኛ ሰላምና እረፍት ያለው ከርሱ ዘንድ ብቻ ነው። ወደ ህይወታችን ስንጋብዘው “ሰላም ለናንተ ይሁን” ብሎ በሰላሙ ያሳርፈናል።

እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግስት ትምጣ ብለን ስንጸልይ በንድ መልኩ የምንጸልየው የእግዚአብሔር ሰላም እንዲመጣ ነው። የግዚአብሔር ሰላም ልብን ይጠብቃል፤ የእግዚአብሔር ሰላም አእሞሮን ያሳርፋል። የሰላም አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page