top of page

ጸሎት አስተምረን -- መንግስትህ ትምጣ —ደስታ (ክፍል ስምንት)

“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፥

ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ

እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... መንግስትህ ትምጣ ...” (ሉቃ. 11፡1-2)

መንግስትህ ትምጣ ብለን ስንጸልይ እየፈልግን ያለነው የግዚአብሔርን ጽድቅ፣ ሰላምና

በመንፈስ ቅዱስ የሚሆንን ደስታ ነው። (ሮሜ 14፡17) ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጽድቅና ሰላም

የሚሉትን ሃሳቦች አይተናል። ዛሬ ደግሞ የእግዚአብሔር መንግስት በመንፈስ ቅዱስ የሚሆን ደስታ

ናት በሚለው ሃሳብ ላይ እናተኩራለን።

የእግዚአብሔርን መንግስት በመፈለግ ጸሎት ውስጥ የሚጠቃለለው አንዱ ሃሳብ በመንፈስ

ቅዱስ የሚሆንን ደስታ መፈለግ ነው። መንግስቱን ስንፈልግ እግዚአብሔር ደስታን ይሰጠናል።

ሰዎች በሚያገኙት ነገር ለተወሰነ ጊዜ ደስ ሊሰጣቸው ይችላል። ነገር ግን በብዙ ጥረትና ድካም

የተገኘ ነገር ለጊዜው ደስ ቢያሰኘም እንኳን ወረቱ ሲያልፍ በሌላ ምኞት ይተካና ያመጣው ደስታ

ይደበዝዛል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰዎች ለመደሰት ሲሉ የተለያየ ሱስና የሃጢያት ልምምድ ውስጥ

ይገባሉ። ነገር ግን ይህም ቢሆን ለጊዜው የሚሰጠው ደስታ ሲያልፍ ትርፉ ጸጸትና ራስ ምታት

ይሆናል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ደስታ ምንጩ መንፈስ ቅዱስ ነው። ደስታው ከውስጥ የሚወጣ

እንጂ በውጪ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ አይደለም። ደስታችን መሰረቱ የሚመጡና የሚሄዱ

ጉዳዮች ሳይሆኑ እግዚአብሔር እራሱ ነው። ለዚህ ነው እምባቆም “ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥

በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ

ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ

አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ” በማለት የተቀኘው። (ዕም. 3:17-18) እምባቆም በውጫዊ ነገሮች

መጉደል ተናውጦና ደስታ ርቆት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔርን በክብሩ ከተመለከተ በኋላ አንድ

እውነት በራለት። ለካስ የደስታ ምንጩ እግዚአብሔር እንጂ የመሙላትና የመጉደል ጉዳይ

አይደለም። እግዚአብሔር ደስታን ያልሰጠው ሰው ሁሉ ሞልቶትም እንኳ እርካታን ያጣል። ለዚህ

ነው መጽሐፍ “ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?” (መክ. 2:25)

የሚለን። ከርሱ ውጪ ደስታ የለም። ሰለሞንም ሁሉን ፈትኖ ደስታን ከሰበሰበው ሃብት፣ ጥበብ፣

ዝናና ተድላ ውስጥ ቢያጣት ጊዜ እግዚአብሔር “ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን

ደስታንም ይሰጠዋል” (መክ. 2:26) በማለት የእውነተኛ ደስታ ምንጩ እርሱ እንደሆነ ተናገረ።

ወገኖቼ፦ ሰው ብዙ የሚደክመው ለመደሰት ነው። ነገር ግን ለሰው የውስጥ ደስታን

የሚሰጠው እግዚአብሔር ብቻ ነው። እርሱ የሚሰጠን ደስታ ኃይላችን ነው። (ነህ. 8:10) በመንግስቱ

ውስጥ ደስታ አለ። እግዚአብሔር ሆይ መንግስትህ ትምጣ። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
spotify-badge-button-listen-wh-BG.png
apple-podcasts-logo.jpg
Google-Podcasts-Badge.jpg
RadioPublicc.png
breaker.png
pocketcasts3.png
Anchor-Podcast-Logo.png

 

5850 N. Elston Avenue 

Chicago, Il 60646

10:00 AM TO 12:00 PM SUNDAY

7:00PM TO 9:00PM FRIDAY

  • Facebook Social Icon
  • Twitter Social Icon
  • Google+ Social Icon
  • YouTube Social  Icon
bottom of page