ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና
“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ
ይጠራል።” (ኢሳ. 9፡6) ከብዙ መቶ አመታት በፊት ነብዩ ኢሳያስ በመንፈስ ተነድቶ ይህንን ታላቅ ትንቢት
ተናገረ። ትንቢቱም በኢየሱስ መወለድ ተፈጸመ። የኢየሱስ መወለድ የፍጥረትን አቅጣጫ የቀየረ ነው። ሕጻን ሆኖ የተወለደው ኢየሱስ “መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ የሆነ ጌታ” ቢሆንም ምድር ልታስተናግደው ስፍራ አልነበራትምና “በግርግም” ተኛ። ነገር ግን በዚያው ቅጽበት ሰማይ እየተደነቀ በዝማሬ ያሸበሽብ ነበር። ብስራቱ አስቀድም ለነገስታት ሳይሆን በሜዳ ላደሩ እረኞች ደረሰ። የምስራች ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት፣ ክርስቶስ ጌታ ተወልዷል የሚል ብስራት ከሰማይ መጣ። ታላቅ የሰማይ ሰራዊት በዝማሬ እግዚአብሔርን አመሰገኑ — ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር፤ ለሰውም በጉ ፈቃድ አሉ። ምድር ያልተቀበለችው ሰማያትን ያስደነቀ ልደት።
ሲወለድ ሰማያት ምልክትን ሰጡ። ሰባ ሰገል ከምስራቅ ኮኮቡን አይተው ሊሰግዱለት መጡ። ንጉስ እንደተወለደ ተረድተው በምሪት መጥተው ወድቀው ሰገዱለት። የከበረ ስጦታቸውንም በፊቱ አቀረቡ። ነገስታት ግን ደነገጡ፣ ፈሩ። እርሱን ለመግደል አስበው የቤተ ልሔምን ሕጻናት ፈጁ። እነ ሄሮድስ የተወለደው “ሕጻን” በስጋ የተገለጠ መለኮት እንደሆነ አልተረዱም። ዮሐንስ ስጋ የሆነው መለኮት ነው ሲል አወጀ። ማቴዎስ የተሰጠን ወንድ ልጅ ሕዝቡን ከኃጢያት የሚያድን እንደሆነ አበሰረ። ለሰው ልጅ የእግዚአብሔርን አብሮነት የሚመልስ — ሰው የጎደለው ክብር የሚመለስበት፤ እግዚአብሔር እንደገና ከሰው ጋር የሚሆንበት የእግዚአብሔር ውድ ስጦታ እንደሆነ ተናገረ። ዮሐንስ እርሱ በጸጋ ላይ ጸጋ ተሞልቶ እንደመጣ አወጀ። በመካከላችንም ያደረው ከሙላቱ ሊያካፍለን እንደሆነ ሰበከ። ነብዩ ኢሳያስ እግዚአብሔር ሕጻን ሆኖ ወደ ምድር የመጣውን አንድ ልጁን እንደሰጠን ወንጌልን አስቀድም በትንቢት ተናገረ። ሕጻን ሆኖ መጥቶ በመካከላችን ያደረው ኢየሱስ አለቅነትን በጫንቃው ላይ የተሸከመ ነው። የምድር ሁሉ ፈጣሪ የሆነ ኃያል አምላክ ነው። የተፈጠረው አለም ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯል፤ አሁንም ጸንቶ ያለው በርሱ የስልጣን ቃል ተደግፎ ነው። የተወለደው ንጉስ ድንቅ መካር ነው። ነፍስን የሚያድን ምክር በርሱ ዘንድ አለ። የአባትነት ሁሉ ምንጭ የሆነ የዘላለም አምላክ ነው። ለተቀበሉትና ላመኑት ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅነትን ስልጣን ያጎናጽፋል። የሰላም ሁሉ ምንጭ የሰላም አለቃ ነው። አለም የማትሰጠውን ሰላም ይሰጣል። መልካም ገና!