top of page

ጸሎት አስተምረን -- ከክፉ አድነን (ክፍል አስራ-አምስት)

“እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ... እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። አላቸውም፦ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... ከክፉ አድነን...” (ሉቃ. 11፡4)

ጌታ ባስተማረን ጸሎት ውስጥ ሌላው የምንጸልየው ጉዳይ መለኮታዊ ጥበቃ ነው። በጸሎቱ ውስጥ እግዚአብሔር ከክፉ እንዲያድነን እንጸልያለን። እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚያድንና የሚጠብቅ አምላክ ነው። በብሉይ ኪዳን እስራዔል በእግዚአብሔር የዳነ እና የሚጠበቅ ሕዝብ ነበር። ቃሉ ስለ እስራዔል ሲናገር “እስራኤል ሆይ፥ ምስጉን ነህ፤ በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማን ነው?” (ዘዳ. 33፡29) ይላል። እስራዔል እግዚአብሔር በጸናች ክንድ ከፈርዖን መንጋጋ ፈልቆቆ ያዳነው ሕዝብ ነው። እስራዔል በማይተኛው በማያንቀላፋው አምላክ የሚጠበቅ ሕዝብ ነው። እንዲሁም በአዲስ ኪዳን እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ ያመንን ሁሉ በጌታ ከኃጢያት የዳንን ሕዝቦች ነን። (“እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” ማቴ. 1፡21) እግዚአብሔር ከሚጠሉንና ከወደረኞቻችን አድኖ ነው ሕዝቡና አገልጋዮቹ ያደረገን። (“ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው።” ሉቃ. 1፡71)

እግዚአብሔር ደግሞ በየእለቱ በዙሪያችን ካሉ የክፋ ፍላጻዎች ሁሉ ይጠብቀናል። ስለዚህም ጥበቃ እንጸልያለን፣ እናመሰግናለንም። በመዝሙር 91 ላይ እንደምናነበው በቀኑ ውስጥ ብዙ ክፋት አለ። በቀኑ ውስጥ የአዳኝ ወጥመድ አለ፣ የሚያስደነግጥ ነገር አለ። በቀኑ ውስጥ የሌሊት ግርማ፣ የሚበር ፍላጻ፣ በጨለማ የሚሄድ ክፉ ነገር፣ አደጋ፣ የቀትር ጋኔን አለ። በቀኑ ውስጥ ተኩላ፣ ዘንዶ፣ እባብ አለ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን እግዚአብሔር በክንፎቹ ጥላ የሚያድሩትን እና በርሱ የሚታመኑትን ይጠብቃቸዋል። ክፉ ነገር ወደ እነርሱ አይቀርብም። ለምን? ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ጥበቃ የተነሳ። ስለዚህ ወገኖቼ ከክፉ አድነን ብለን ስንጸልይ ክንፎችህ በኛ ላይ ይዘርጉ ማለታችን ነው። እርሱን ተስፋና መጠጊያ ማድረጋችን ነው። በልዑል መጠጊያ መኖራችን ነው። እርሱን መታመኛና መሸሸጊያ ማድረጋችን ነው። ያን ጊዜ እርሱ ይከበናል፣ ይጋርደናል። በአጠገባችን ሺ፣ በቀኛችንም አስር ሺ ቢወድቅም ወደኛ ግን አይቀርብም።

ወገኖቼ፦ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? እርሱ በዙሪያችን አጥር ከሆነልን ማን ያገኘናል? እርሱ ከወደደን ምን ያሰጋናል? ዘማሪው እንደ ዘመረው ወዶናልና አዳነን። ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣን። የምናመልከው አምላክ የሚያድን አምላክ ነው። እርሱ ከሚፋጅ እሳት ያድናል። እርሱ ከወጥመድ ያድናል። በየቀኑ ከብዙ ከምናውቃቸውና ከማናውቃቸው የክፋት ፍላጻዎች አድኖናል። ወደፊትም ደግም ያድነናል። የኛ መታመኛ የእርሱ ጥበቃ፣ የእርሱ እጅ ነው እንጂ የኛ ብልሃት አይደለም። በእርሱ ካለን ማንም እውሬ ከእጁ ሊነጥቀን አይችልም። እርሱ የበጎች ታላቅ እረኛ ነው። እርሱ የማይተኛ፣ የማያንቀላፋ፣ ኃይሉ የማይደክም ብርቱ እረኛ ነው። አባታችን ሆይ ከክፉ አድነን። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page