ጸሎት አስተምረን -- ኃይል ለዘላለም የእግዚአብሔር ነው (ክፍል አስራ-ሰባት)
“እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ... መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን።” (ማቴ. 6፡13)
የአባታችን ሆይ ጸሎት የግዚአብሔርን ስም በመቀደስና መንግስቱን በመፈለግ ይጀምራል። ደግሞም የግዚአብሔርን ዘላለማዊ መንግስት፣ ዘላለማዊ ኃይልና ዘላለማዊ ክብር በማወጅ ይጠቃለላል። ባለፈው ሳምንት እንዳየነው አሁን በምንኖርበት አለም ብዙ መንግስታት ቢኖሩም ሁሉን አሸንፎ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው የእግዚአብሔር መንግስት ነው። የመንግስት ጽናትና ጥንካሬ ባለው ኃይል ላይ የተመሰረተ ነው። የእግዚአብሔር መንግስት የእግዚአብሔር ኃይል የሚገለጥበት ነው።
የእግዚአብሔር ኃይል ዘላለማዊ ነው። በአለማችን ታሪክ ብዙ ኃያላን መንግስታት ተነስተዋል። ባቢሎን ኃያል ነበር። ፐርሺያ ኃያል ነበር። ክሪክ ኃያል ነበር። ግብጽ ኃያል ነበር። ወደ ቅርብ ግዜ ታሪክ ስንመጣ ደግሞ እነ ስፔን፣ ፓርቱጋልና ብሪታኒያ ኃያላን ነበሩ። እነኚህ ኃያላን በጊዜአቸው አለምን ያንቀጠቀጡ ቢሆንም አሁን ግን “ነበሩ” በማለት ታሪካቸውን እንዘክራለን። እግዚአብሔር ግን ሁልጊዜ በዙፋኑ ላይ አለ። እርሱ ኃይሉ አይደክምም፤ ማስተዋሉም አይመረመርም። ኢሳያስ በኖረበት ዘመን ብርቱ የነበረው ዖዚያን በሞተበት ጊዜ ነብዩ በሃዘን ሳይመታ እንዳልቀረ ይገመታል። ነገር ግን በዚያው አመት ኢሳያስ እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየው። ነገስታት ቢለዋወጡም፤ ጊዜ ቢያልፍም እርሱ በዙፋኑ ላይ በኃይሉ ይኖራል።
በታሪክ የእግዚአብሔር ኃይል በልዩ ልዩ መንገድ ተገልጿል። ፍጥረት በራሱ የእግዚአብሔርን ኃይል ያሳየናል። ሐዋሪያው ጳውሎስ እንዳስተማረን የእግዚአብሔር “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።” ፍጥረትን ተምልክተን የእግዚአብሔርን ኃይልና ታላቅነት አለማድነቅ አንችልም። ሰው እንኳን በራሱ አስደናቂ ፍጥረት ነው። የእያንዳንዳችን የጣት አሻራ የተለያየ ነው። በውስጣችን ያለው መላዘር (DNA) ቢዘረጋ 10 ቢሊዮን ማይልስ ርዝመት ይኖረዋል። ፍትረተ-አለም ከምንረዳው በላይ ረቂቅና ትልቅ ነው። ለዚህ ነው ዘማሪው ሲዘምር “ስራው እንዲህ ያማረለት እርሱማ አንዴት ውብ ነው” በማለት የተቀኘው።
የእግዚአብሔር የብርታቱ ጉልበት የተገለጠው በፍጥረት ስራ ውስጥ ሳይሆን በማዳን ስራ ውስጥ ነው። ሐዋሪያው ጳውሎስ እንደጻፈልን እግዚአብሔር ክርስቶስን “ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል።” ክርስቶስ ከሙታን ሲነሳ ሞት ተረትቷል። ሰይጣን ስልጣኑ ተገፏል። እግዚአብሔር ብቻ ለዘላለም ኃያል እንደሆነ በሰማይና በምድር ሁሉ ተረጋግጧል። አባታችን ሆይ ኃይል ለዘላለሙ ያንተ ነው። አሜን!