top of page

ከሁሉም የሚበልጠው ማንነት!

“ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።” (2ቆሮ 5፡17)

ከጥቂት ጊዜ በፊት አልፍሬድ ፖስቴል ስለሚባል አንድ ሰው አነበብኩኝ። ሚስተር ፖስቴል አሁን ቤት-የለሽ (homeless) እና የአእምሮ እመምተኛ ነው። ሚስተር ፖስቴል በጣም የተማረና ትልቅ ስራ የነበረው ሰው ነው። ከታዋቂው የሃርቫርድ ዩኒቭርሲቲ የሕግ ዲግሪ ተቀብሏል። እንዲሁም የኢኮኖሚክስና የአካውንቲንግ ዲግሪዎች አሉት። በጣም ታዊቂ ከሆኑ ሰዎች ጋር (የአሁኑን የአሜሪካን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ ጨምሮ) አብሮ የመማር እድል ነበረው። በጊዜውም ትልቅ ደሞዝ እየተከፈለው ለታወቀ የሕግ ድርጅት ይሰራ ነበር። ነገር ግን በሕይወቱ በገጠመው ሳንካ የተነሳ አሁን በኑሮ የመጨረሻ ጠርዝ ላይ ይገኛል።

የሚስተር ፓስቴልን ህይወት ያነበበ ሁሉ ስለ ማንነቱና ስለ ህይወቱ ትርጉም ማሰቡ አይቀርም። ማንነታችንን ባለን የትምህርት ደረጃ፣ ስራ፣ የገንዘብ ሃብት፣ ማህበራዊ ስፍራ አንጻር የምንመዝን ከሆነ አስተማማኝ መሰረት ላይ አልቆምንም። እንኚህ ሁሉ በቀላሉ የሚሸረሽሩና የሚያልፉ ነገሮች ናቸው። ነገር ግን እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ከዘር፣ ከቋንቋ፣ ከትምህርት ደረጃ፣ ከሃብት፣ ከማህበራዊ ስፍራ ... ወዘተ ያለፈ ማንነት ሰጥቶናል። ቃሉ “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁ” (ገላ. 3፡28) ይለናል። እንዲሁም ቃሉ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ እንደሚል፤ ትምክህት ካስፈለገ የምንመካበት ማንነት በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነው ማንነት ነው። ይህ ማንነት ነው ምድራዊውን ተሻግሮ ለሰማያዊ ርስት የሚያበቃን። ይህ ማንነት ነው በምድርም ስንኖር የማያቋርጥ የሰላም ምንጭ የሚሆነን። ለዚህ ነው ቃሉ በሌላ በምንም ሳይሆን በጌታ ደስ ይበላችሁ የሚለን። በሌሎችን ነገሮች ለጥቂት ጊዜ ደስ መሰኘት ይቻል ይሆናል። ዘላቂ የውስጥ ሃሴት የሚገኘው ግን በጌታ ላይ ባለን ማንነት ብቻ ነው።

ይህንን ጉዳይ በጥልቀት የተረዱ የእምነት አባቶች ምድራዊውን ነገር ንቀው በተፈጠሩበት ዘላቂ ማንነት ኖሩ። ለዚህ መቼም ከሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ የሚበልጥ አብነት የለንም። እርሱ በምድር ባሉ የክብር መለኪያዎች ተወዳዳሪ አልነበረውም። በትውልድ የቢንያም ወገን ነው፣ እብራዊ ነው፣ ፈሪሳዊ ነው፣ ከገማልያል እግር ስር ቁጭ ብሎ የተማረ የሕግ አዋቂ ነው። ነገር ግን ይህንን ሁሉ ክርስቶስን ከማወቅ ጋር ሲያነጻጽረው እንደ ጉዳትና እንደ ጉድፍ እቆጥረዋለሁ ይላል። (“አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ” ፊሊ. 3፡ 8-9)። የእምነት አባት ሙሴም ስለሚበልጠው በክርስቶስ ስላለው ክብር የግብጽን ባለጠግነትና ክብር እንቢ ብሎ ከወገኖቹ ጋር መክራ መቀበልን መረጠ። ለምን ቢሉ በአለም (“በግብጽ”) ካለው ማንነት ይልቅ በክርስቶ ያለው ማንነት እጅግ የከበረና የበለጠ እንደሆነ ስለተረዳ ነው። ወገኖቼ፦ የሚስተር ፓስቴልን ሕይወት ስናንብ በእርግጥም በዓለም ያለ ማንነትና ክብር በቅጽበት የሚለወጥና የሚጠፋ ነው፤ ምድራዊና ጊዚያዊም ነው። የሚጸናው በክርስቶስ ያገኘነው ማንነት ነውና በዚያ እንኑር!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page