ሥራህ ምንድር ነው?
“...ሥራህ ምንድር ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ ወዴት ነው? ወይስ ከማን ወገን ነህ? አሉት። እርሱም፦ እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ አላቸው።” (ዮናስ 1፡8-9)
ብዙ ሰው ስራህ ምንድን ነው ተብሎ ሲጠየቅ “እኔ መሃንዲስ ነኝ”፤ “እኔ ሃኪም ነኝ”፤ “እኔ ሼፍ ነኝ” ወይንም እንዲህና እንዲያ ነኝ ብሎ ይመልሳል። ይህ ጥያቄ ለነብዩ ዮናስ አንድ ጊዜ ቀርቦለት ነበር። በትንቢተ ዮናስ ላይ እንደምናነበው ዮናስ እግዚአብሔር ወደ ነነዌ ሊልከው ወዶ ሳለ እርሱ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ኮብልሎ የተርሴስ መርከብ ተሳፍሮ ሲሄድ እግዚአብሔር በባህሩ ላይ ታላቅ መናወጥን አመጣ፤ መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች። የሚደንቀው ነገር ዮናስ ከእግዚአብሔር ሊኮበልል ማሰቡ ነው። ማንም ከእግዚአብሔር መኮብለል የሚችል የለም። እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው። መዝሙረኛው ዳዊት አንድ ጊዜ እንደዚህ ዘመረ፡ ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች። በውኑ ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትሆናለች፤ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና፤ እንደ ጨለማዋ እንዲሁ ብርሃንዋ ነው። (መዝ. 139፡7-12) ከእግዚአብሔር መንፈስ የትም መሰወር አይቻልም። ይልቁንም ለኛ የሚሻለን ወደ እርሱ መጠጋት ነው።
ዮናስ ሊኮበልል ፈለገ ነገር ግን አልቻለም። ዮናስን ለማግኘት እግግዚአብሔር ባህሩን አናወጠ። መርከቧ ተጨነቀች። ዮናስ ግን በመርከባ የውስጠኛው ክፍል ተኝቶ ነበር። ዮናስ በተገኘ ጊዜና ይህ ታላቅ መከራ ያገኛቸው በእርሱ ምክንያት እንደሆነ ሲገነዘቡ በመርከቧ የነበሩት አዛዦች አምላኩ ስለርሱ ባህርን የሚያናውጥ ይህ ምን አይነት ሰው ነው ብለው የተገረሙ ይመስላሉ። ስለዚህም ጥያቄ ጠየቁት፡ “ሥራህ ምንድር ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ ወዴት ነው? ወይስ ከማን ወገን ነህ?” ጥያቄው የማንነትና የአላማ ጥያቄ ነበር። አገርና ወገን ማንነትን ይገልጣል፤ ስራ ደግም አላማን ይወክላል። ዮናስ የሰጠው መልስ ግሩም ነበር። እኔ እብራዊ ነኝ። ስራዬም እግዚአብሔርን ማምለክ ነው ብሎ መለሰ። ሃገሬ፣ ትውልዴ ማንነቴ ሁሉ የተጠቀለለው በእብራዊነቴ ውስጥ ነው ማለቱ ነው። የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ህዝብ ወገን ነኝ፤ ማንነቴ ያለው ከእግዚአብሔር ጋር ባለኝ ግንኙነት ውስጥ ነው ማለቱ ነው። የተፈጠርኩበት ዋናው አላማ ደግሞ እግዚአብሔርን ማምለክ ነው ማለቱ ነው። ወገኖቼ፦ እኛ የእግዚአብሔር ወገኖች ነን። የሕይወታችን ትርጉም ያለው ከርሱ ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ ነው። የመኖራችን ዋናው አላማም አምልኮ — እግዚአብሔር ማምለክ ነው። እግዚአብሔር ህዝቡን በጸናች ክንድ ከግብጽ ያወጣው፤ ባለንበት ዘመን ደግም በመስቀል ጣር የወለደው ያመልከው ዘንድ ነው።