የእግዚአብሔርን መንግሥት መፈለግ—2
“ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ
ይጨመርላችኋል።” (ማቴ. 6:33)
ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 14 ቁጥር 17 ላይ እንደገለጻት "የእግዚአብሔር መንግሥት
ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት።” ስለዚህ የእግዚአብሔር መንግስት አሁን በመካከላችን
የመንግስቱ ጽድቅ፣ ሰላምና ደስታ ሲገለጽ በስራ ላይ ነች ማለት ነው። ባለፈው ሳምንት የመንግስቱን ጽድቅ
ተመልክተናል። ዛሬ በመግስቱ ሰላምና ደስታ ላይ እናተኩራለን።
የእግዚአብሔር መንግስት ወንጌል ሰላም ይሰጣል። ጌታ ኢየሱስ በቃሉ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥
ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም”
ብሎናል (ዮሐ. 14:27)። ከቃሉ እንደምናስተውለው ሁለት አይነት ሰላም አለ። አለም የሚሰጠው በጊዚያዊ
ነገሮችን ላይ የተመሰረተ ሰላም አለ፤ ደግሞም ጌታ የሚሰጠው ሰላም አለ። አለም የሚሰጠው ሰላም
ውጪያዊ ነው። ከውጭ ባሉ ነገሮች ሁኔታ የሚወሰን ነው። የጌታ ሰላም ግን ከውስጥ የሆነ ሰላም ነው።
በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በእርጋታ እንድንቀመጥ የሚያደርገን የእግዚአብሔር ሰላም ነው። ስለሆነም
የእግዚአብሔር ሰላም በአለም እንዳለው ሰላም የነውጥ አለመኖር ብቻ ሳይሆን ዙሪአችን ነውጥ ቢኖርም
እንኳ በእርጋታ መቀመጥ ማለት ነው። የእግዚአብሔር ሰላም ሲኖረን ልባችን አይታወክም፣ አይፈራም።
ስለዚህ ነው ዘማሪው “ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም” ያለው
(መዝ. 46፡2)። የሰላማችን ምንጭ እግዚአብሔር እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። በማንኛውም ሁኔታ በጸሎትና
በልመና ከምስጋናም ጋር ወደ እርሱ ስንቀርብ እርሱ አእሞሮን ሁሉ በሚያልፍ ሰላም ልባችንና ሃሳባችንን
ይጠብቃል (ፊል. 4:7)። በመከራ መኃል፣ በችግር መኃል፣ በነውጥ መኃል አዕሞሮአችን በሰላም የተጠበቀ
ነው። እውነተኛ ሰላምና እረፍት ያለው የሰላም አለቃ ከሆነው ከጌታ ዘንድ ብቻ ነው። ወደ ህይወታችን
ስንጋብዘው “ሰላም ለናንተ ይሁን” ብሎ በሰላሙ ያሳርፈናል። የግዚአብሔር ሰላም ልብን ይጠብቃል፤
የእግዚአብሔር ሰላም አእሞሮን ያሳርፋል። ክርስቶስ ኢየሱስ ሸክማቸው የከበደውን ወደ እርሱ
የሚመጡትን ሁሉ በሰላሙ ያሳርፋል።
መንግስቱን ስንፈልግ እግዚአብሔር ደስታን ይሰጠናል። ሰዎች በሚያገኙት ነገር ለተወሰነ ጊዜ ደስ
ሊላቸው ይችላል። ነገር ግን በብዙ ጥረትና ድካም የተገኘ ነገር ለጊዜው ደስ ቢያሰኘም እንኳን ወረቱ
ሲያልፍ በሌላ ምኞት ይተካና ያመጣው ደስታ ይደበዝዛል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰዎች ለመደሰት ሲሉ
የተለያየ ሱስና የሃጢያት ልምምድ ውስጥ ይገባሉ። ነገር ግን ይህም ቢሆን ለጊዜው የሚሰጠው ደስታ
ሲያልፍ ትርፉ ጸጸትና ራስ ምታት ይሆናል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ደስታ ምንጩ መንፈስ ቅዱስ ነው።
ደስታው ከውስጥ የሚወጣ እንጂ በውጪ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ አይደለም። ደስታችን መሰረቱ
የሚመጡና የሚሄዱ ጉዳዮች ሳይሆኑ እግዚአብሔር እራሱ ነው። ለዚህ ነው እምባቆም “ምንም እንኳ
በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥
በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ
አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ” በማለት የተቀኘው (ዕም. 3:17-18)። እምባቆም በውጫዊ ነገሮች መጉደል
ተናውጦና ደስታ ርቆት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔርን በክብሩ ከተመለከተ በኋላ ደስታ ምንጩ
እግዚአብሔር እንጂ የነገሮች መሙላትና መጉደል እንዳልሆነ ተረዳ። እግዚአብሔር ደስታን ያልሰጠው ሰው
ሁሉ ሞልቶትም እንኳ እርካታን ያጣል። ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ “ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም
ተድላን የቀመሰ ማን ነው?” (መክ. 2:25) የሚለን። ከርሱ ውጪ ደስታ የለም። ንጉስ ሰለሞንም ሁሉን
ፈትኖ ደስታን ከሰበሰበው ሃብት፣ ጥበብ፣ ዝናና ተድላ ውስጥ ቢያጣት ጊዜ እግዚአብሔር “ደስ
ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን ደስታንም ይሰጠዋል” (መክ. 2:26) በማለት የእውነተኛ ደስታ
ምንጩ እርሱ እንደሆነ ተናገረ። ሰው ብዙ የሚደክመው ለመደሰት ነው ነገር ግን ለሰው የውስጥ ደስታን
የሚሰጠው እግዚአብሔር ብቻ ነው። የግዚአብሔር መንግስት በመካከላችን ስትሰራ የእግዚአብሔር ጽድቅ፣
ሰላምና ደስታ ይገለጣል።