የሙሴ እናት
“ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፥ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው።... እኅቱም ለፈርዖን ልጅ፦ ሕፃኑን ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን? አለቻት። የፈርዖንም ልጅ፦ ሂጂ አለቻት፤ ብላቴናይቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች።” (ዘጸ. 2፡ 3፣ 7፣ 8)
ሙሴ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው። ስለሙሴ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ” ይለናል (ዕብ. 11:24) ሙሴ የፈርዖን (የንጉስ) የልጅ ልጅ እንዳይባል እንቢ ያለው አይኖቹ ተከፍተውለት የሚበልጥን ክብር ለማየት ስለቻለ ነው። ቃሉ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይለናል፡ “ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና” (ቁ. 25)። ሙሴ በፊቱ ምርጫ ነበር በአንድ በኩል የግብጽ ብዙ ሃብት፣ ክብርና ዝና አለ። በሌላ በኩል ደግም ስለ ክርስቶስ መነቀፍና ከእግዚአብሔር ህዝብ ጋር መከራ መቀበል አለ። ሙሴ የሁለቱንም ምርጫዎች ብድራት ትኩር ብሎ ተመልክቶ በመረዳት ከእግዚአብሔር ህዝብ ጋር መሆንን መረጠ። ለምድራዊ ሰው የሙሴ ምርጫ ማስተዋል ያለበት አይመስልም። አይኖቹ የተከፈቱለት ሰው ግን ሙሴ የመረጠው የሚበልጠውን እንደሆነ ይረዳል። ሙሴ በብሉይ ኪዳን የኖረ ሰው ቢሆንም በሩቁ ሆኖ ክርስቶስን ለማየት የቻለ ሰው ነው። ስለዚህ ነው ቃሉ “ስለ ክርስቶስ መነቀፍ” እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንደሆነ አሰበ የሚለን። ሙሴ ክርስቶስን መረጠ።
ነገር ግን በሙሴ ላይ የነበረው የእግዚአብሔር አላማ እንደተጠበቀ ሆኖ በህይወቱ ላይ ታላቅ አስተዋኦ ያደረገችው እናቱ ናት። በመጀመሪያ ወንድ ሁሉ ይገደል የሚለውን የፈርዖንን አዋጅ ሳትፈራ ህጻኑን ሶስት ወር ሸሸገችው። ይህንን ስታደርግ “ሕጻኑ መልካም እንደሆነ” አይታ ነው። ይህ መልካምነት የውጪ ውበት ብቻ ሳይሆን (በእርግጥ ህጻን ሁሉ ያማረ ነውና) በሕጻኑ ላይ ያለውን አምላካዊ አላማ የተረዳች እንደሆነ እናስተውላለን። ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ ደግሞ እጅግ ብልሃት በተሞላበት መንገድ ለህጻኑ ልዩ መንሳፈፊያ ሰርታ የንጉስ ልጅ በምትመጣበት አካባቢ አስቀመጠችው። ይህም ብቻ ሳይሆን በህጻኑ እህት በኩል በልጁ ላይ የሚሆነውን ትከታተል ነበር።
ሙሴን ተንከባክባ ያሳደገችው እናቱ ነች። ሙሴን ስታሳድግ እናቱ አካላዊ እንክብካቤ ብቻ ሳይሆን ያደረገችለት ለህይወት ዘመኑ ሁሉ የሆነ መረዳትም እንዲኖረው አድርጋ ነው ያሳደገችው። ስለማንነቱ (የተመረጠ የእግዚአብሔር ህዝብ እንደሆነ)፣ እግዚአብሔር በህዝቡ ላይ አላማ እንዳለው፣ እርሱ እንደማንኛው አይነት ልጅ ሳይሆን የእግዚአብሔር አላማ ያለበት እንደሆነ አስተምራዋለች። ስለዚም ሙሴ ምንም እንኳ በንጉስ ቤት የንጉስን ስርዓት የተማረ ቢሆንም እናቱ የመራችው መንገድ ግን በጥሪው እንዲሄድ ትልቅ እገዛ ሆኖታል። ስለዚህ ባደገ ጊዜ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እንቢ አለ። ውስጡ የተቀመጠው እውነት የአለምን ክብርና ዝና ንቆ ለእግዚአብሔር አላማ የተለየ ህይወት እንዲኖር አደረገው።
እንደ ሙሴ እናት ሁሉ ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን አካላዊ እንክብካቤ በማድረግ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር መንገድ በመምራት ትውልድን የማትረፍና የመቅረጽ ስራ ይሰራሉ። ከእግዚአብሔር መንግስት አንጻር ደግሞ ሁላችንም በቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በአደራ ለሰጠን ልጆች አሳዳጊና ወላጆች ነን። ለእናቶች ሁሉ መልካም የእናቶች ቀን እንላለን። እግዚአብሔር ይባርካችሁ።