በእምነት መቅረብ
“ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።” (ዕብ. 11፡ 6)
አባታችን ሄኖክ በትውልዱ መካከል ለየት ያለ ሰው እንደነበረ መጽሐፍ ያስተምረናል።የትውልዶችን የዘር ሃረግ የያዘውን ዘፍጥረት ምዕራፍ ሰድስትን ስናነብ የብዙ አባቶች ህይወት የተዘገበው“እገሌ ይህን ያህል አመት ኖረ፣ ወንድኖችና ሴቶች ልጆችን ወለደ፣ ሞተም” እየተባለ ነው። ነገር ግን ሄኖክ ላይ ስንደርስ አተራረኩ ለየት ይላል። ስለ ሄኖክ ሲናገር “ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ...ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፣ እግዚአብሔር ወስዶታልና” በማለት በትውልዶች መካከል ለየት ያለውን የሄኖክን ሕይወት መጽሐፍ ይተርክልናል። (ዘፍ. 5፡21-24) የዕብራዊያን ጸሓፊ ደግም ሄኖክ እካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው እንዴት እንደሆነ በመንፈስ ቅዱስ ብረሃን ያስረዳናል። (ዕብ. 11፡ 5-6)
ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው በእምነት በመመላለስ ነበር። በእምነቱ እግዚአብሕሔርን ደስ አሰኝቷል። ከዚህም የተነሳ በምነት የሚገኝ ሕይወት ምሳሌ ሆኖ ሞትን አልቀመሰም። በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ፍጻሚያቸው ሞት ነበር። ሄኖክ ግን “ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ።” ሄኖክ በዘመኑ ሞትን ሳይቀምስ የተወሰደው በእግዚአብሔር ላይ ከነበረው እምነት የተነሳ ነው። ወገኖቼ፦ ዛሬም በክርስቶስ በማመን ከሞት ወደ ሕይወት በተሸጋገርን በኛ ላይ ሞት ስልጣን የለውም። የሄኖክ እምነት በሕወቱ ላይ ለውጥ ያመጣ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርም ደስ የተሰኘበት እምነት ነበር። መቼም መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናጠና ከምንረዳው ቁም ነገር አንዱና ዋንኛው እግዚአብሔር እርሱን አምነው በሚመላለሱ ሰዎች እንዴት ደስ እንደሚሰኝ ነው። ለዚህ ዋቤ ይሆነን ዘንድ በእብራዊያን ምዕራፍ 11 የተዘረዘሩትን የእምነት አርበኞች ማስታወሱ በቂ ነው። ጌታ ኢየሱስም በምድር ሲመላለስ አስደንቀውት ከነበሩት ነገሮች አንዱና ዋንኛው ባልጠበቀው ስፍራ በሰዎች ያገኘው እምነት ወይንም ሊያምኑ በተገባቸው ሰዎች ያጣው እምነት ነበር። ለመሆኑ ከአባታችን ሄኖክ እምነት የምንማረው ምንድን ነው?
የሄኖክ እምነት መሰረታዊ አስተምሮ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር እንዳለ ያምን ዘንድ እንደሚያስፈልገውና እግዚአብሔርም በእምነት ለሚፈልጉት ዋጋ እንዲሚሰጥ ማመን ናቸው። ይህ አይንቱ እምነት የእግዚአብሔርን ሕልውና የመቀበል ጉዳይ ብቻ አይደለም። ብዙ ሰዎች (ሰይጣንም ጭምር) እግዚአብሔር እንዳለ ግንዛቤ ወይንም እውቀት አላቸው። ነገር ግን ያ እወቀት ሕይወታቸውን (ልባቸውን) የሚገራ እውቀት ሳይሆን የአእምሮ እውቀት ብቻ ነው። ከሄኖክ የምንማረው እምነት ግን ከዚህ የሚያልፍ ነው። ሄኖክ እግዚአብሔር እንዳለ ሲያምን እግዚአብሔርን በሚፈልገው ጉዳይ እንዳለ ነው የሚያምነው። በጤናው ላይ እግዚአብሐርን ሲያምን እግዚአብሔር ፋዋሽ አምላክ እንደሆነና እንደሚፈሰው ነው የሚያምነው። በፋይናንሱ ላይ እግዚአብሔርን ሲያምን እግዚአብሔር የሚባርክ አምላክ እንደሆነና ሊባርከው እንደሚችል ነው የሚያምነው። በጥበቃው ላይ እግዚአብሔርን ሲያምን እግዚአብሔር እንደሚጠብቀውና ከአውሬና ከክፉ ወጥመድ ሁሉ እንደሚታደገው ነው የሚያምነው። እንግዲህ ሄኖክ ያመነው የእግዚአብሔርን ሕልውና፣ አዳኝነት፣ ፈዋሽነት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር እርሱን በፈለገበት ቢዚያ ማንነቱ እንደሚገለጥለትና ዋጋም እንደሚሰጠው ጭምር ነው።
ወገኞቼ፦ ክርስትና የእምነት ጉዞ ነው። ወደ እግዚአብሔር የምንቀርበውና እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኘው በእምነት ብቻ ነው። ዛሬ በማናቸውም በፊታችን ባለ ጉዳይ ላይ እግዚአብሔርን እየፈለንግ እርሱን በፈለግንበት አቅጣጫ ሁሉ ላይ ዋጋ እንደሚሰጠን በማመን እንመላለስ። አሜን!