ኢየሱስ ይወዶታል!
ፍቅር ጥልቅ ነገር ነው። ፍቅር አያስገድድም ነገር ግን ብርቱ ገፊ ነው። ከያኒያን ዜማን ከግጥም አዋህደው፤ ቀለም በቡርሽ አጣቅሰው፤ ድርሰት ከምናብ አፍልቀውና ምስል ከድምጽ አቀናብረው ስለ ፍቅር ጥልቀት፣ ጥንካሬና ውበት ይቀኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስም የፍቅርን ኃይል ሲገልጽ “ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናትና ... ብዙ ውኃ ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልም” ይላል። (መኃ 8፡ 6-7) እግዚአብሔርም ሰውን የወደደበት ፍቅር እጅግ ብርቱና ጥልቅ ነው። እግዚአብሔር አንድ ልጁን ለመስቀል ሞት አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ሰውን ሁሉ ወዷል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ፍቅር “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” በማለት ይገልጸዋል (ዮሐ. 3፡16) ይህ ፍቅር እርሶንም የሚጠቀልል ነው። እግዚአብሔር እኛ በሕይወት እንኖር ዘንድ ሃጢያት የማያውቀውን አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለኛ በደል በመስቀል እንዲደቅና እንዲሞት በመፍቀድ ለእኛ ያለውን ወሰን የሌለውን ፍቅሩን አሳይቷል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል የሞተው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የለየውን የኃጢያት ግድግዳ በሞቱ አፍርሶ ለሚያምን ሁሉ የሚሆን የደህንነትን መንገድ ለማበጀት ነው። እግዚአብሔር ሰውን በምሳሌው ፈጥሮ እንዲበዛና ምድርን እንዲሞላት፣ ምድርንም እንዲገዛና እንዲያስተዳድር ባርኮት፣ ከእርሱም ጋር ሕብረትን እያደረገ በገነት እንዲኖር በክብር ስፍራ አስቀምጦት ነበር። ነገር ግን ሰው በዲያቢሎስ ተንኮል ተታሎ የፈጣሪውን ትዕዛዝ በመተላለፍ መንፈሳዊ ሞትን ሞተ። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ኃጢያት ገባ። ከዚያም በኋላ የተከተለው የአዳም ትውልድ ሁሉ በኃጢያት ስር ወደቀ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” ይለናል። (ሮሜ 3፡23) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ኃጢአት በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም ገባ። የኃጢያት ዋጋ ወይንም ውጤት ሞት ሰለሆነ በኃጢአትም በኩል ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።
ጌታችን ኢየሱስ ከቅድስት ድንግል ማሪያም ተወልዶ በመስቀል ላይ የሞተው በኃጢያት ምክንያት የመጣብንን የሞት ፍዳ ለመክፈል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የአለምን ኃጢያት ሁሉ ተሸክሞ በመስቀል ላይ በመዋል፣ ስጋው ተቆርሶ፣ ደሙ ፈሶ ለአለም ሁሉ የሚሆን የደህንነት ቤዛ ሆኗል። በክርቶስም መስቀል በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የለየው ኃጢያት፣ በኃጢያትም ምክንያት በሰው ላይ ነግሶ የነበረው ሞት ተነስቷል። እግዚአብሔር በባህሪው ፍጹም ጻዲቅ ፍጹምም መሃሪ በመሆኑ የክርስቶስ ሞት የኃጢያትን ቅጣት በመክፈል የእግዚአብሐርን ጽድቅ ፈጸመ። የክርስቶስ ትንሳዔ ደግሞ የእግዚአብሔርን ምህረትና የማዳን ኃይል በመግለጽ ሙታን ለነበርን ለኛ የድነት መንገድ ሆነ። ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነን በሞቱና በትንሳኤው ስንተባበር ለኃጢያት ሞተን ለጽድቅ ህያዋን እንሆናለን።