top of page

ፈልጉ

“ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴ. 6:33)

በዚህ በላይ በሰፈረው ክፍል እግዚአብሔር መለኮታዊውን ቅደም-ተከተል በቃሉ ገልጾልናል። ቅዱሳን ለኑሮ በሚያስፈልግ መብልና መጠጥ፤ ልብስና መጠለያ እንጨነቅ ዘንድ የእግዚአብሔር ሃሳብ አይደለም። የዚህ አለም ሰዎች የሚኖሩበት ቅደም ተከተል በመጀምሪያ ህይወትን ለማሰንበት የሚያስፈልገውን ነገር መፈለግ ነው። ለክርሲቲያን ግን ቅድሚያ መሆን ያለበት ሕይወትን ራሷን የሰጠንን ጌታና አምላክ መፈለግ ነው። ያም ደግም በልጁ የተገለጸውን ጽድቁን እንዲሁም እርሱ የሚገዛበትን መንግስት በመፈለግ ይገለጻል።

መፈለግ የሚጀምረው በልብ ካለ ስፍራ ነው። በልባችን የመጀመሪያውን ስፍራ የሰጠነው ነገር ያንቀሳቅሰናል። መቅደላዊት ማሪያም ጌታ በስሞን ቤት እንዳለ ሰማች። ከዚያም ምንም እንኳ ተጋባዥ ታዳሚ ባትሆንም ያለበት ስፍራ ድረስ ፈልጋ ሄደች። ካገኘችውም በኋላ የከበረ አልብስጥሮስ ሽቶዋን ሰብራ እራሱ ላይ አፈሰሰች። ከዚያም እግሩ ላይ ወደቀችና አመልከችው። መፈለግ እንዲህ ነው። በመኃልይ 1:7 ላይ ሱናማይቱ ሴት “ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፤ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ስለ ምንስ ከባልንጀሮችህ መንጎች በኋላ እቅበዘበዛለሁ?” እያለች ውዷን ትፈልገዋለች። ወዴት ነህ ትለዋለች። በእርግጥ ፀሃይ ያጥቁራት እንጂ እስትታገኘው መፈለግዋን አልተወችም።

እግዚአብሔርን መፈለግ ማለት እግዚአብሔርን በልባችን አንደኛ ማድረግ ነው። እርሱን በልባችን ዙፋን ላይ መሾም ነው። እግዚአብብሔር እስራኤልን እንዲህ ይለዋል፦ “እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” (ዘዳ. 6፡ 4-5)። የእግዚአብሔር መንግስትና የእግዚአብሔር ጽድቅ (እግዚአብሔር እራሱ) በልባችን የመጀመሪያውን ስፍራ ሲይዝ ነው እግዚአብሔርን የምናመልከው። ያንን ስፍራ ሌላ ማንም ሊይዘው አይገባም። ያንን ስፍራ ሌላ ከያዘው ጣኦት ነው።

መፈለግ ዋጋን ከመስጠት ጋር ይያያዛል። የእግዚአብሔር መንግስት የከበረ መንግስት ነች። በምንም አትለካም፤ ከምንም ጋር አትስተካከልም። በማቴዎስ 11፡ 44 – 46 ላይ እንደምናነበው የእግዚአብሔር መንግስት “በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፥ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ።” እንዲሁም ደግሞ “መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።” በነዚህ ምሳሌዎች የምንረዳው የእግዚአብሔር መንግስት እጅግ የከበረች እንደሆነች እና ለመንግስቱ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጀን ወይንም መንግስቱን በምንም ዋጋ ልንለውጠው እንደማንችል ነው።

በመጨረሻም መንግስትቱንና ጽድቁን መፈለግ ማለት መንግስቱና ጽድቁ በህወታችን እንዲሰራና እንድገለጥ መፈለግ ማለት ነው። እንግዲህ የእግዚአብሔርን መንግስት ስንሻ የምንፈልገው የመንግስቱን ጽድቅ፣ ሰላምና ደስታ ነው። ተጽኖዋን ነው የምንፈልገው። መንግስቱ በተጽኖ የምትገለጥ ነችና እንደ ዘር ታድጋለች፣ እንደ እርሾ ታቦካለች፣ እንደ ብርሃን ታበራለች፣ እንደ ጨው ታሰማለች። ወገኖች አስቀድመን የእግዚአብሔርን መግስት ጽድቁንም እንፈልግ ሌላው ሁሉ ይጨመርልናል። አሜን!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page