top of page

መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪው መንፈስ

“መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ።” (መዝ. 104:30)

መጽሐፍ ቅዱስ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሲያስተዋውቀን እርሱ ከአብና ከወልድ ጋር በመፍጠር ስራ ላይ ነበር። በፍጥረት ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ “በውኃ ላይ ሰፍፎ” ነበር። መንፈስ ቅዱስ ባዶ ለነበረች፣ አንዳችም ላልነበረባት፣ በጨለማ ለነበረች ምድር ሙላት፣ ቅርጽ፣ ብርሃንና ውበት ሲያበጅ እናያለን። ስለዚም መዝሙረኛው “መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ” በማለት ተቀኝቷል (መዝ. 104:30)። መንፈስ ቅዱስ ለሰማያት ውበትን የሰጠ እርሱ ነው። እዮብ ይህንኑ ሲገልጽ “በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ፥ እጁም በራሪይቱን እባብ ወጋች” (እዮብ 26:13) ይላል።

መንፈስ ቅዱስ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው። እኛም አዲስ ልደት ያገኘነው ሙት የነበረውን ማንነታችንን መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ስለሰጠው ነው። ለዚህ ነው ጌታችን ለኒቆዲሞስ ዳግም ስለ መወለድ ሲገልጽለት “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ያለው (ዮሐ. 3:5)። ዳግመኛ የተወለድነው በእግዚአብሔር ቃልና በመንፈስ ቅዱስ ነው። ውሃ የቃሉ ምሳሌ ነው። ውሃ እንደሚያነጻና የሕይወት መሰረት እንደሆነ ሁሉ ቃሉም እንዲሁ ነው። ስለዚህ ዳግመኛ የተወልድነው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በእግዚአብሔር ቃል ነው። ይህንኑ ሐዋሪያው ጴጥሮስ “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ” (1ጴጥ. 1:23) በማለት ያጸናልናል። በቲቶም ላይ ይንንኑ እናነባለን፡ “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን” (3:5)።

እንዲሁም ደግሞ በንትሳኤ በአዲስ ሰውነት የሚያስነሳን መንፈስ ቅዱስ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ሐዋሪያው ጳውሎስ ሲያስተምር “ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል” (ሮሜ 8:11) ብሏል። አሁን በኛ ውስጥ ያለው ቅዱሱ መንፈስ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሳው መንፈስ ነው። ለእኛም ሟች ስጋ ደግሞ ሕይወትን የሚሰጠው እርሱ ነው። ለዚህም በመንፈስ ቅዱስ የዘላለም ሕይወት ዋስትናን አግኝተናል። ለቤዛ ቀን የታተምነው በዚሁ መንፈስ ነው። አሁንም የመንፈስን ጥንካሬ የሚሰጠን፤ ሞት ሞት የሸተተውን ሕይወታችንን በሕይወት ጠረን የለወጠው እርሱ ነው።

ወግኖቼ፦ ቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጣሪ ነው። ለምድር ቅርጽ፣ ውበትና ሙላት የሰጠ እርሱ ነው። ለኛም ሙት ለነበርነው ሕይወትን የሰጠን እርሱ ነው። ዛሬም ወደ እርሱ የበለጠ ስንቀርብ ሕይወታችንን ያስውባል፣ በስጦታዎቹ ይሞላናል፣ አቅጣጫን ይሰጠናል። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።


Recent Posts
Archive
Search By Tags
No tags yet.
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
spotify-badge-button-listen-wh-BG.png
apple-podcasts-logo.jpg
Google-Podcasts-Badge.jpg
RadioPublicc.png
breaker.png
pocketcasts3.png
Anchor-Podcast-Logo.png

 

5850 N. Elston Avenue 

Chicago, Il 60646

10:00 AM TO 12:00 PM SUNDAY

7:00PM TO 9:00PM FRIDAY

  • Facebook Social Icon
  • Twitter Social Icon
  • Google+ Social Icon
  • YouTube Social  Icon
bottom of page