top of page

ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል።

“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” (ኢሳ. 9፡6)

ከብዙ መቶ አመታት በፊት ነብዩ ኢሳያስ በመንፈስ ተነድቶ ይህንን ታላቅ ትንቢት ተናገረ። ትንቢቱም በኢየሱስ መወለድ ተፈጸመ። የኢየሱስ መወለድ የፍጥረትን አቅጣጫ የቀየረ ነው። ሕጻን ሆኖ የተወለደው ኢየሱስ “መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ የሆነ ጌታ” ቢሆንም ምድር ልታስተናግደው ስፍራ አልነበራትምና “በግርግም” ተኛ። ነገር ግን በዚያው ቅጽበት ሰማይ እየተደነቀ በዝማሬ ያሸበሽብ ነበር። ብስራቱ አስቀድም ለነገስታት ሳይሆን በሜዳ ላደሩ እረኞች ደረሰ። የምስራች ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት፣ ክርስቶስ ጌታ ተወልዷል የሚል ብስራት ከሰማይ መጣ። ታላቅ የሰማይ ሰራዊት በዝማሬ እግዚአብሔርን አመሰገኑ — ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር፤ ለሰውም በጉ ፈቃድ አሉ። ምድር ያልተቀበለችው ሰማያትን ያስደነቀ ልደት።

ሲወለድ ሰማያት ምልክትን ሰጡ። ሰባ ሰገል ከምስራቅ ኮኮቡን አይተው ሊሰግዱለት መጡ። ንጉስ እንደተወለደ ተረድተው በምሪት መጥተው ወድቀው ሰገዱለት። የከበረ ስጦታቸውንም በፊቱ አቀረቡ። ነገስታት ግን ደነገጡ፣ ፈሩ። እርሱን ለመግደል አስበው የቤተ ልሔምን ሕጻናት ፈጁ። እነ ሄሮድስ የተወለደው “ሕጻን” በስጋ የተገለጠ መለኮት እንደሆነ አልተረዱም። ዮሐንስ ስጋ የሆነው መለኮት ነው ሲል አወጀ። ማቴዎስ የተሰጠን ወንድ ልጅ ሕዝቡን ከኃጢያት የሚያድን እንደሆነ አበሰረ። ለሰው ልጅ የእግዚአብሔርን አብሮነት የሚመልስ — ሰው የጎደለው ክብር የሚመለስበት፤ እግዚአብሔር እንደገና ከሰው ጋር የሚሆንበት የእግዚአብሔር ውድ ስጦታ እንደሆነ ተናገረ። ዮሐንስ እርሱ በጸጋ ላይ ጸጋ ተሞልቶ እንደመጣ አወጀ። በመካከላችንም ያደረው ከሙላቱ ሊያካፍለን እንደሆነ ሰበከ። ነብዩ ኢሳያስ እግዚአብሔር ሕጻን ሆኖ ወደ ምድር የመጣውን አንድ ልጁን እንደሰጠን ወንጌልን አስቀድም በትንቢት ተናገረ። ሕጻን ሆኖ መጥቶ በመካከላችን ያደረው ኢየሱስ አለቅነትን በጫንቃው ላይ የተሸከመ ነው። የምድር ሁሉ ፈጣሪ የሆነ ኃያል አምላክ ነው። የተፈጠረው አለም ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯል፤ አሁንም ጸንቶ ያለው በርሱ የስልጣን ቃል ተደግፎ ነው። የተወለደው ንጉስ ድንቅ መካር ነው። ነፍስን የሚያድን ምክር በርሱ ዘንድ አለ። የአባትነት ሁሉ ምንጭ የሆነ የዘላለም አምላክ ነው። ለተቀበሉትና ላመኑት ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅነትን ስልጣን ያጎናጽፋል። የሰላም ሁሉ ምንጭ የሰላም አለቃ ነው። አለም የማትሰጠውን ሰላም ይሰጣል።

በመካከላችን ያደረው ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የዓለም ብርሃን ነው። ስለዚህ ጉዳይ ወንጌል ሲናገር “በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም” ይለናል። (ዮሐ. 1፡ 4-5) አህዛብ ሁላችን ያለ ክርስቶስ ተስፋ አጥተን በጨለማ የተቀመጥን ነበርን። ነገር ግን በጨላማ ተቀምጠን ለነበርነው ለኛ ታላቅ ብርሃን መጣልን። በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጥን ለኛ ብርሃን ወጣልን። ይህ በወንጌል ያገኘነው ብርሃን የእግዚአብሔር ብርሃን ነው። እግዚአብሔር በጨለማችን ላይ “ብርሃን ይብራ” ብሎ የልባችንን ጨለማ ገፎታል። እኛንም የብርሃን ልጆች አድርጎን ለአለም የምናበራ የአለም ብርሃን እንድሆን ሾሞናል።መልካም ገና!


Recent Posts
Archive
Search By Tags
Follow Us
  • Facebook Basic Square
  • Twitter Basic Square
  • Google+ Basic Square
bottom of page