እግዚአብሔር እረኛዬ ነው -- ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ።
የእግዚአብሔር እረኝነት ከሚገለጥበት መንገድ አንዱ መሪነቱ ነው። እረኛ በጎቹን እንደሚመራቸው ሁሉ ጌታም ይመራናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን ስለ እውነተኛ እረኛ ሲናገር በመጀምሪያ እውነተኛ እረኛ መለያው የእርሱ የሆኑት በጎች ድምጹን ለይተው ያውቁታል፤ ደግሞም ይሰሙታል (ዮሐ. 10:3-4)። በጎቹ የእረኛቸውን ድምጽ ከለሌላ ድምጽ ጋር አያምታቱም። ይህ እንግዲህ የሚሆነው በበጎቹና በእረኛው መካከል ተግባቦትና ትውውቅ እንዲሁም በመቀራራብ የተወለደ መታመን ስላለ ነው። እረኛው ለበጎቹ ድምጹን ካሰማ በኋላ በስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል (ቁ. 3)። ከዛም ከፊታቸው ይሄዳል። እንግዲህ ይህ መልካም እረኛ የሚመራው ከፊት በመሄድ ነው እንጂ ከኋላ በመንዳት አይደለም። እረኛችን እግዚአብሔር ከፊት እየሄደ የሚመራ ነው። እኛም ደግም ድምጹን ስለምናውቅ እንከተለዋለን።
የእግዚአብሔር መሪነት የሚጀምረው ነፍሳችንን ከማዳን ነው። ዳዊት በዚህ ስፍራ ሁለት ነገሮችን ያነሳል። አንደኛ “ነፍሴን መለሳት” ይላል። ሁለተኛ ደግም “ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ” ይላል። መመለስ ያለበት የጠፋ፣ የተቅበዘበዘና ከመንገድ የወጣ ነው። ጌታ ኢየሱስ የመጣው የጠፋውንና የባዘነውን ፍለጋ ነው። ይህንንም በቃሉ “የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና” (ማቴ. 18:11) በማለት ያረጋግጥልናል። እግዚአብሔር የጠፋው ሲገኝ፣ የባዘነው ሲመለስ ደስ ይለዋል። ለዚህም ነው የጠፋነውን ፍለጋ ልጁን የላከው።ስለሆነምእግዚአብሔር እርሱየሕዝቡ እረኛ መሆኑን ይገልጽና እኔ “የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ” ይላል (ሕዝ. 34:16)። እንግዲህ የእግዚአብሔር መሪነት የተገለጸው በመጀመሪያ የጠፋችውን ነፍሳችንን በመመለስ ነው። ጌታችንም የመጣው ከጥፋት መንገዳቸን መልሶ ሊባርከን ነው። ስለዚህም ቃሉ “ለእናንተ አስቀድሞ እግዚአብሔር ብላቴናውን አስነሥቶ፥ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ እየመለሰ ይባርካችሁ ዘንድ፥ ሰደደው” (ሐዋ. 3:26)። እረኛችን እግዚአብሔር ነፍሳችንን መልሷታል፣ አድኗታል። ስሙ ለዘላለም የተባረከ ይሁን።
እግዝዚአብሔር ነፍሳችንን ከጥፋት መልሶ አልተወንም ነገር ግን በጽድቅ መንገድ ደግሞ መርቶናል። እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የሰጠን ቤዛነትን ብቻ ሳይሆን ጽድቅና ቅድስናንም ሰጥንቶናል። አስቀድም በከንቱነት እየተመላለስን ነበር። ነገር ግን አሁን ቃሉ እንደሚያስተምረን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥበናል፣ ተቀድሰናል፣ ጸድቀናል (1ቆሮ. 6:11)። ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ጥበብ፣ ጽድቅ፣ ቅድስናና ቤዛ ሆኖልናል። ስለዚህ እረኛችን ካዳነንና ከቀደሰን፣ በተቀበልነው በዚህ አዲስ ማንነት መመላለስ ግድ ይለናል። ደግሞም አምላካችን ይህንን ቸርነት ያደረገልን ስለ እኛ ማንነት ወይንም በኛ ዘንድ ስለተገኘ በጎነት ሳይሆን “ስለ ስሙ” ነው። የዳነው የክብሩ ምስጋን እንሆን ዘንድ ነው። በፊታችን ባለው ዘመንም እግዚአብሔር ስለ ስሙ ያጸናናል። ቃሉ “እግዚአብሔር ለእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ወድዶአልና እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም” (1ሳሙ. 12:22) እንደሚል እግዚአብሔር የስሙ ክብር ይመሰገን ዘንድ አዳነን ደግሞም በጽድቅ መንገድ መራን።
ወገኖቼ፦ ያዳነንና ያጸደቀን ጌታ አሁንም በየእለቱ ይመራናል፣ ከፊታችን ይወጣል። እኛ ግን ሁል ጊዜ ድምጹን መሻት አለብን። ድምጹ ደግሞ በቃሉ በኩል፣ በጸሎት ስፍራችን፣ እንዲሁም በቅዱሳን ሕብረት ወደ እኛ ይፈሳል። አሜን!